አገሩ የእኛ ነው፣ ከጥንት ጀምሮም የእኛ ነበር፡፡ ከእነሱ ይልቅ እኛ በአገሩ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ኖረናል፡፡ ከእነሱ በተሻለም እኛ በምድሩ ላይ ሠርተናል፣ ደክመናል፡፡ እኛ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ከምድሩ ጋር ያለን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ግንኙነት ከአይሁዶች በጣም ይልቃል፡፡ ስለዚህ እነሱ ለምድሩ አለን የሚሉት ጥንታዊ ታሪካዊ መብት አገሩን የመውሰድ መብት አይሰጣቸውም፡፡ በተመሣሣይመልኩ እኛም አረቦች በጥንታዊ ቤታችን ስፔይን ላይ ያለንን ታሪካዊ መብት መጠየቅ አንችልም፡፡ ስፔይን በእኛ በአረቦች ለስምንት ምዕተ ዓመታት ያህል በተዳደረችበት ወቅት ገናና ከመሆኗም በተጨማሪ ለዘመናዊው የአውሮፓ ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ ሁናለች፡፡